الرعد

Ar-Ra'd

ሱራ 13 · መዲና · 43 አንቀጾች · የወረደበት ቅደም ተከተል፦ 96

ጽሕፈት
ትርጉሞች

ንባቡን፣ አወቃቀሩንና ሥሩን ለማየት የዐረብኛ ቃል ይንኩ።

بِسْمِ ٱللَّهِ ٱلرَّحْمَٰنِ ٱلرَّحِيمِ
  1. Sadiq & Sani Habibአ.ለ.መ.ረ (አሊፍ ላም ሚም ራ) ይህች (አናቅጽ) ከመጽሐፉ አንቀጾች ናት፡፡ ያም ከጌታህ ወዳንተ የተወረደው እውነት ነው፡፡ ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች አያምኑም፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibአላህ ያ ሰማያትን የምታዩዋት አዕማድ ሳትኖር ያነሳት ከዚያም በዐርሹ (ዙፋኑ) ላይ (ስልጣኑ) የተደላደለ ፀሐይንና ጨረቃንም የገራ ነው፡፡ ሁሉም ለተወሰነ ጊዜ ይሮጣሉ፡፡ ነገሩን ሁሉ ያስተናብራል፡፡ በጌታችሁ መገናኘት ታረጋግጡ ዘንድ ተዓምራቶችን ይዘረዝራል፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibእርሱም ያ ምድርን የዘረጋ በሷም ተራራዎችንና ወንዞችን ያደረገ በውስጧም ከፍሬዎች ሁሉ ሁለት ሁለት ዓይነቶችን ያደረገ ነው፡፡ ሌሊትን በቀን ይሸፍናል፡፡ በዚህም ውስጥ ለሚያስተነትኑ ሕዝቦች ምልክቶች አሉ፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibበምድርም የተጎራበቱ ቁርጥራጮች አልሉ፡፡ ከወይኖችም አትክልቶች አዝርዕቶችም መንታዎችና መንታዎች ያልኾኑ ዘንባባዎችም አልሉ፡፡ በአንድ ውሃ ይጠጣሉ፤ (በጣዕምም ይለያያሉ)፡፡ ከፊሉዋንም በከፊሉ ላይ በሚበላው ሰብል እናበልጣለን፡፡ በዚህም ውስጥ ለሚያውቁ ሕዝቦች ተዓምራት አለበት፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibብትደነቅም ዐፈር በኾንን ጊዜ እና አዲስ ፍጥረት እንኾናለን ማለታቸው (ታላቅ) ድንቅ ነው፡፡ እነዚህ እነዚያ በጌታቸው የካዱት ናቸው፡፡ እነዚህም እንዛዝላዎች በአንገቶቻቸው ላይ ያሉባቸው ናቸው፡፡ እነዚሀም የእሳት ጓዶች ናቸው፡፡ እነሱ በውስጧ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibከእነሱ በፊት የመሰሎቻቸው ቅጣቶች በእርግጥ ያለፉ ሲኾኑ ከመልካሙ በፊት በመጥፎው ያስቸኩሉሃል፡፡ ጌታህም ለሰዎች ከመበደላቸው ጋር በእርግጥ የምህረት ባለቤት ነው፡፡ ጌታህም በእርግጥ ቅጣተ ብርቱ ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibእነዚያም የካዱት በእርሱ ላይ ከጌታው ተዓምር ለምን አልተወረደለትም ይላሉ፡፡ አንተ አስፈራሪ ብቻ ነህ፡፡ ለሕዝብም ሁሉ መሪ አላቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibአላህ ሴት ሁሉ የምታረግዘውን ያውቃል፡፡ ማሕጸኖችም የሚያጎድሉትን የሚጨምሩትንም (ያውቃል)፡፡ ነገሩም ሁሉ እርሱ ዘንድ በልክ የተወሰነ ነው፡፤
  1. Sadiq & Sani Habibሩቁንና ቅርቡን ዐዋቂ ታላቅ የላቀ ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibከእናንተ ውስጥ ቃሉን ዝቅ ያደረገ ሰው በእርሱ የጮኸም ሰው እርሱ በሌሊት ተደባቂም በቀን (ተገልጾ) ኺያጅም የኾነ ሰው (እርሱ ዘንድ) እኩል ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibለእርሱ (ለሰው) ከስተፊቱም ከኋላውም በአላህ ትዕዛዝ (ከክፉ) የሚጠብቁት ተተካኪዎች (መላእክት) አሉት፡፡ አላህ በሕዝቦች ዘንድ ያለውን ጸጋ በነፍሶቻቸው ያለውን (ኹኔታ) እስከሚለውጡ ድረስ አይለውጥም፡፡ አላህም በሰዎች ላይ ክፉን በሻ ጊዜ ለእርሱ መመለስ የለውም፡፡ ለእነርሱም ከእርሱ ሌላ ምንም ተከላካይ የላቸውም፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibእርሱ ያ የምትፈሩና የምትከጅሉም ስትሆኑ ብልጭታን የሚያሳያችሁ ከባዶች ደመናዎችንም የሚያስገኝ ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibነጎድጓድም አላህን በማመስገን ያጠራል፡፡ መላእክትም እርሱን ለመፍራት (ያጠሩታል)፡፡ መብረቆችንም ይልካል፡፡ እነርሱም (ከሓዲዎች) በአላህ የሚከራከሩ ሲሆኑ በእርሷ የሚሻውን ሰው ይመታል፡፡ እርሱም ኀይለ ብርቱ ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibለእርሱ (ለአላህ) የእውነት መጥሪያ አለው፡፡ እነዚያም ከእርሱ ሌላ የሚገዙዋቸው (ጣዖታት) ወደ አፉ ይደርስ ዘንድ ወደ ውሃ መዳፎቹን (በሩቅ ሆኖ) እንደሚዘረጋ (ሰው መልስ) እንጂ ለነርሱ በምንም አይመልሱላቸውም፡፡ እርሱም ወደ አፉ ደራሽ አይደለም፡፡ የከሓዲዎችም ጥሪ በከንቱ እንጂ አይደለም፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibበሰማያትና በምድርም ያሉት ሁሉ በውድም ሆነ በግድ ለአላህ ይሰግዳሉ፡ ጥላዎቻቸውም በጧቶችና በሠርኮች ይሰግዳሉ፡፡
  1. Sadiq & Sani Habib«የሰማያትና የምድር ጌታ ማን ነው» በላቸው፡፡ «አላህ ነው» በል፡፡ «ለነፍሶቻቸው ጥቅምንም ጉዳትንም የማይችሉን ረዳቶች ከርሱ ሌላ ያዛችሁን» በላቸው፡፡ «ዕውርና የሚያይ ይስተካከላሉን ወይስ ጨለማዎችና ብርሃን ይስተካከላሉን ወይስ ለአላህ እንደርሱ አፈጣጠር የፈጠሩን ተጋሪዎች አደረጉለትና ፍጥረቱ በእነሱ ላይ ተመሳሰለባቸውን» በል፤ «አላህ ሁለመናውን ፈጣሪ ነው፡፡ እርሱም አንዱ አሸናፊው ነው» በል፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibከሰማይ ውሃን አወረደ፡፡ ሸለቆዎቹም በመጠናቸው ፈሰሱ፡፡ ጎርፉም አሰፋፊውን ኮረፋት ተሸከመ፡፡ ለጌጥ ወይም ለዕቃ ፍላጎት በእርሱ ላይ እሳት የሚያነዱበትም (ማዕድን) ብጤው የኾነ ኮረፋት አልለው፡፡ እንደዚሁ አላህ ለእውነትና ለውሸት ምሳሌን ያደርጋል፡፡ ኮረፋቱማ ግብስብስ ኾኖ ይጠፋል፡፡ ለሰዎች የሚጠቅመውማ በምድር ላይ ይቆያል፡፡ እንደዚሁ አላህ ምሳሌዎችን ይገልፃል፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibለእነዚያ ለጌታቸው ለታዘዙት መልካም ነገር (ገነት) አልላቸው፡፡ እነዚያም ለእርሱ ያልታዘዙት ለእነሱ በምድር ያለው ሁሉ ከእርሱም ጋር ብጤው ቢኖራቸው ኖሮ በእርሱ በተበዡበት ነበር፡፡ እነዚያ ለእነሱ ክፉ ምርመራ አለባቸው፡፡ መኖሪያቸውም ገሀነም ናት፡፡ ፍራሻቸውም ከፋች!
  1. Sadiq & Sani Habibከጌታህ ወዳንተ የተወረደው እውነት መኾኑን የሚያውቅ ሰው እንደዚያ እርሱ ዕውር እንደኾነው ሰው ነውን የሚገሠጹት የአእምሮ ባለቤቶች ብቻ ናቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibእነዚያ በአላህ ቃል ኪዳን የሚሞሉ የጠበቀውንም ኪዳን የማያፈርሱ ናቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibእነዚያም አላህ እንዲቀጠል በእርሱ ያዘዘውን ነገር የሚቀጥሉ ጌታቸውንም የሚያከብሩ መጥፎንም ቁጥጥር የሚፈሩ ናቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibእነዚያም የጌታቸውን ውዴታ ለመፈለግ የታገሱ፣ ሶላትንም አዘውትረው የሰገዱ፣ እኛ ከሰጠናቸው ሲሳይም በምስጢርም ኾነ በግልጽ የመጸወቱ፣ ክፉውንም ነገር በበጎ የሚገፈትሩ ናቸው፡፡ እነዚያ ለእነሱ መጨረሻይቱ ምስጉን አገር አለቻቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habib(እርሷም) የመኖሪያ ገነቶች ናት፡፡ ይገቡባታል፡፡ ከአባቶቻቸውም፣ ከሚስቶቻቸውም፣ ከዝርያቸውም መልካም የሠራ ሰው (ይገባታል)፡፡ መላእክትም በእነርሱ ላይ ከየደጃፉ ሁሉ ይገባሉ፡፡
  1. Sadiq & Sani Habib«ሰላም ለእናንተ ይኹን፡፡ (ይህ ምንዳ) በመታገሳችሁ ነው፡፡ የመጨረሻይቱም አገር ምን ታምር!» (ይሏቸዋል)፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibእነዚያም የአላህን ቃል ኪዳን ከጠበቀ በኋላ የሚያፈርሱ አላህም እንዲቀጠል በእርሱ ያዘዘውን ነገር የሚቆርጡ በምድርም ላይ የሚያበላሹ እነዚያ ለነሱ እርግማን አለባቸው፡፡ ለእነሱም መጥፎ አገር (ገሀነም) አላቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibአላህ ለሚሻው ሰው ሲሳይን ያሰፋል፤ ያጠባልም፡፡ (ከሓዲዎች) በቅርቢቱም ሕይወት ተደሰቱ፡፡ የቅርቢቱም ሕይወት በመጨረሻይቱ አንጻር (ትንሽ) መጠቀሚያ እንጂ ምንም አይደለችም፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibእነዚያም የካዱት «በእርሱ ላይ ከጌታው ተዓምር ለምን አልተወረደም» ይላሉ፡፡ «አላህ የሚሻውን ያጠምማል፡፡ የተመለሰውንም ሰው ወደርሱ ይመራል» በላቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habib(እነሱም) እነዚያ ያመኑ ልቦቻቸውም አላህን በማውሳት የሚረኩ ናቸው፡፡ ንቁ! አላህን በማውሳት ልቦች ይረካሉ፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibእነዚያ ያመኑትና መልካም ሥራዎችን የሠሩት ለእነሱ ደግ ኑሮ መልካም መመለሻም አላቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibእንደዚሁ ከበፊትዋ ብዙ ሕዝቦች በእርግጥ ያለፉ ወደኾነችው ሕዝብ እነርሱ በአልረሕማን የሚክዱ ሲኾኑ ያንን ወደ አንተ ያወረድነውን ቁርኣን በእነርሱ ላይ ታነብላቸው ዘንድ ላክንህ፡፡ «እርሱ (አልረሕማን) ጌታዬ ነው፡፡ ከእርሱ ሌላ አምላክ የለም፡፡ በርሱ ላይ ተጠጋሁ፡፡ መመለሻየም ወደርሱ ብቻ ነው» በላቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibቁርኣንም በእርሱ ተራራዎች በተነዱበት ወይም በእርሱ ምድር በተቆራረጠችበት ወይም በእርሱ ሙታን እንዲናገሩ በተደረጉበት ኖሮ (የመካ ከሓዲዎች ባላመኑ ነበር)፡፡ በእውነቱ ነገሩ ሁሉ የአላህ ነው፡፡ እነዚያ ያመኑት ሰዎች እነሆ አላህ በሻ ኖሮ ሰዎችን በመላ በእርግጥ ይመራቸው እንደነበረ አያውቁምን እነዚያም የካዱት በሥራቸው ምክንያት (አጥፊ) ዐደጋ የምታገኛቸው ከመኾን ወይም የአላህ ቀጠሮ እስኪመጣ በአገራቸው አቅራቢያ (አንተ) የምትሰፍርባቸው ከመኾን አይወገዱም፡፡ አላህ ቀጠሮውን አያፈርስምና፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibከአንተ በፊት በነበሩትም መልክተኞች በእርግጥ ተላግጦባቸዋል፡፡ ለእነዚያም ለካዱት ጊዜን ሰጠኋቸው፡፡ ከዚያም (በቅጣት) ያዝኩዋቸው፡፡ ቅጣቴም እንዴት ነበር!
  1. Sadiq & Sani Habibእርሱ በነፍስ ሁሉ ላይ በሠራቸው ሥራ ተጠባባቂ የኾነው (አላህ እንደዚህ እንዳልኾነው ጣዖት ብጤ ነውን) ለአላህም ተጋሪዎችን አደረጉ፡፡ ጥሯቸው «አላህን በምድር ውስጥ የማያውቀው ኖሮ ትነግሩታላችሁን ወይስ ከቃል በግልጽ (ፍቺ በሌለው ከንቱ ቃል ተጋሪዎች በማለት ትጠሩዋቸዋላችሁን)» በላቸው፡፡ በእውነቱ ለእነዚያ ለካዱት ተንኮላቸው ተሸለመላቸው፡፡ ከእውነቱ መንገድም ታገዱ፡፡ አላህም ያጠመመው ሰው ለእርሱ ምንም አቅኚ የለውም፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibለእነሱ በቅርቢቱ ሕይወት ቅጣት አላቸው፡፡ የመጨረሻይቱም (ዓለም) ቅጣት በጣም የበረታ ነው፡፡ ለእነሱም ከአላህ (ቅጣት) ምንም ጠባቂ የላቸውም፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibያች ጥንቁቆቹ ተስፋ የተሰጧት ገነት ምጣኔዋ (እንደሚነገራችሁ ነው)፡፡ ከሥርዋ ወንዞች ይፈስሳሉ፡፡ ምግቧ (ሁልጊዜ) የማይቋረጥ፤ ነው፡፡ ጥላዋም (እንደዚሁ)፡፡ ይህች የእነዚያ የተጠነቀቁት መጨረሻ ናት፡፡ የከሃዲዎችም መጨረሻ እሳት ናት፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibእነዚያም መጽሐፉን የሰጠናቸው ወዳንተ በተወረደው ይደሰታሉ፡፡ ከአሕዛብም ከፊሉን የሚክዱ ሰዎች አልሉ፡፡ «እኔ የታዘዝኩት አላህን ብቻ እንድገዛ በእርሱም እንደዳላጋራ ነው፡፡ ወደእርሱ እጠራለሁ፤ መመለሻዬም ወደእርሱ ነው» በላቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibእንደዚሁ በዐረብኛ የተነገረ ፍትሕ ሲኾን አወረድነው፡፡ ዕውቀቱ ከመጣልህም በኋላ ዝንባሌዎቻቸውን ብትከተል ከአላህ ቅጣት ምንም ረዳትም ጠባቂም የለህም፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibከአንተ በፊትም መልክተኞችን በእርግጥ ልከናል፡፡ ለእነርሱም ሚስቶችንና ልጆችን አድርገናል፡፡ ለማንኛውም መልክተኛ በአላህ ፈቃድ እንጂ ተዓምር ሊያመጣ አይገባውም፡፡ ለጊዜው ሁሉ ጽሑፍ አለው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibአላህ የሚሻውን ያብሳል፤ ያጸድቃልም፡፡ የመጽሐፉ መሠረትም እርሱ ዘንድ ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibየዚያንም ያስፈራራናቸውን ከፊሉን ብናሳይህ (መልካም ነው)፡፡ ወይም ብንገድልህ (ወቀሳ የለብህም)፡፡ በአንተ ላይ ያለብህ ማድረስ ብቻ ነው፡፡ ምርመራውም በኛ ላይ ነው፡፤
  1. Sadiq & Sani Habibእኛ ምድርን ከጫፎችዋ የምናጎድላት ኾነን የምንመጣባት መኾናችንን አላዩምን አላህም ይፈርዳል፡፡ ለፍርዱም ገልባጭ የለውም፡፡ እርሱም ምርመራው ፈጣን ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibእነዚያም ከእነሱ በፊት የነበሩት በእርግጥ መከሩ፡፡ አዘንግቶም የመያዙ ዘዴ በሙሉ የአላህ ነው፡፡ ነፍስ ሁሉ የምትሠራውን ያውቃል፡፡ ከሓዲዎችም የመጨረሻይቱ አገር ለማን እንደምትኾን ወደፊት ያውቃሉ፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibእነዚያም የካዱት ሰዎች «መልክተኛ አይደለህም» ይላሉ፡፡ «በእኔና በእናንተ መካከል መስካሪ በአላህና እርሱ ዘንድ የመጽሐፉ ዕውቀት ባለው ሰው በቃ» በላቸው፡፡