التوبة

At-Tawbah

ሱራ 9 · መዲና · 129 አንቀጾች · የወረደበት ቅደም ተከተል፦ 113

ጽሕፈት
ትርጉሞች

ንባቡን፣ አወቃቀሩንና ሥሩን ለማየት የዐረብኛ ቃል ይንኩ።

  1. Sadiq & Sani Habib(ይህች) ከአላህና ከመልክተኛው ወደእነዚያ ቃል ኪዳን ወደ ተጋባችኋቸው አጋሪዎች የምትደርስ ንጽሕና ናት፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibበምድር ላይም አራት ወሮችን (ጸጥተኞች ስትኾኑ) ኺዱ፡፡ እናንተም ከአላህ (ቅጣት) የማታመልጡ መኾናችሁንና አላህም ከሓዲዎችን አዋራጅ መኾኑን ዕወቁ፤ (በሏቸው)፡፡
  1. Sadiq & Sani Habib(ይህ) ከአላህና ከመልክተኛው በታላቁ ሐጅ ቀን የወጣ አላህ ከአጋሪዎቹ ንጹሕ ነው መልክተኛውም (እንደዚሁ)፡፡ (ከክህደት) ብትጸጸቱም እርሱ ለእናንተ በላጭ ነው፡፡ (ከእምነት) ብትሸሹም እናንተ አላህን የማታቅቱት መኾናችሁን ዕወቁ በማለት ወደ ሰዎች የሚደርስ ማስታወቂያ ነው፡፡ እነዚያን የካዱትንም በአሳማሚ ቅጣት አብስራቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibከአጋሪዎቹ እነዚያ ቃል ኪዳን የተጋባችኋቸውና ከዚያም ምንም ያላጎደሉባችሁ በናንተ ላይም አንድንም ያልረዱባችሁ ሲቀሩ፤ (እነዚህን) ቃል ኪዳናቸውን እስከጊዜያታቸው (መጨረሻ) ሙሉላቸው፡፡ አላህ ጥንቁቆችን ይወዳልና፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibየተከበሩትም ወሮች ባለቁ ጊዜ አጋሪዎቹን በአገኛችሁባቸው ስፍራ ግደሉዋቸው፡፡ ያዙዋቸውም፣ ክበቡዋቸውም፣ ለእነሱም (መጠባበቅ) በየመንገዱ ተቀመጡ፡፡ ቢጸጸቱም፣ ሶላትንም በደንቡ ቢሰግዱ፣ ግዴታ ምጽዋትንም ቢሰጡ መንገዳቸውን ልቀቁላቸው፡፡ አላህ መሓሪ አዛኝ ነውና፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibከአጋሪዎችም አንዱ ጥገኝነትን ቢጠይቅ የአላህን ቃል ይሰማ ዘንድ አስጠጋው፡፡ ከዚያም ወደ መጠበቂያው ስፍራ አድርሰው፡፡ ይህ እነሱ የማያውቁ ሕዝቦች በመኾናቸው ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibለአጋሪዎቹ አላህ ዘንድና እመልክተኛው ዘንድ ቃል ኪዳን እንዴት ይኖራቸዋል እነዚያ በተከበረው መስጊድ ዘንድ ቃል ኪዳን የተጋባችኋቸው ብቻ ሲቀሩ፡፡ (እነዚህ) በቃል ኪዳናቸው ለእናንተ ቀጥ እስካሉላችሁ ድረስ ለነርሱም ቀጥ በሉላቸው፡፡ አላህ ጥንቁቆችን ይወዳልና፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibበእናንተ ላይ ቢያይሉም በእናንተ ውስጥ ዝምድናንና ቃል ኪዳንን የማይጠብቁ ሲኾኑ እንዴት (ቃል ኪዳን ይኖራቸዋል)፡፡ በአፎቻቸው ያስወድዷችኋል፡፡ ልቦቻቸውም እንቢ ይላሉ፡፡ አብዛኞቻቸውም አመጸኞች ናቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibበአላህ አንቀጾች ጥቂትን ዋጋ ገዙ፡፡ ከመንገዱም አገዱ፡፡ እነርሱ ይሠሩት የነበሩት ሥራ ከፋ!
  1. Sadiq & Sani Habibበምእምን ነገር ዝምድናንም ኪዳንንም አይጠብቁም፤ እነዚያም እነሱ ወሰን አላፊዎች ናቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibቢጸጸቱም፣ ሶላትንም ቢሰግዱ፣ ዘካንም ቢሰጡ የሃይማኖት ወንድሞቻችሁ ናቸው፡፡ ለሚያውቁ ሕዝቦችም አንቀጾችን እናብራራለን፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibከቃል ኪዳናቸው በኋላ መሓላዎቻቸውን ቢያፈርሱ፣ ሃይማኖታችሁንም ቢያነውሩ፣ የክህደት መሪዎችን (ከክህደት) ይከለከሉ ዘንድ ተዋጉዋቸው፡፡ እነርሱ ቃል ኪዳን የላቸውምና፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibመሓላዎቻቸውን ያፈረሱትን መልክተኛውንም ለማውጣት ያሰቡትን ሕዝቦች እነሱ ለመጀመሪያ ጊዜ የጀመሩዋችሁ ሲኾኑ ለምን አትዋጉዋቸውም ትፈሩዋቸዋላችሁን ምእምናን እንደ ኾናችሁም አላህ ይበልጥ ልትፈሩት የተገባው ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibተጋደሉዋቸው፡፡ አላህ በእጆቻችሁ ያሰቃያቸዋል፡፡ ያዋርዳቸዋልም፡፡ በእነሱም ላይ ይረዳችኋል፡፡ የምእምናን ሕዝቦችንም ልቦች ያሽራል፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibየልቦቻችሁንም ቁጭት ያስወግዳል፡፡ አላህም ከሚሻው ሰው ላይ ጸጸትን ይቀበላል፡፡ አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibእነዚያን ከእናንተ ውስጥ የታገሉትንና ከአላህም ከመልክተኛውም ከምእመናንም ሌላ ምስጢረኛ ወዳጅ ያልያዙትን አላህ ሳይገልጽ ልትተው ታስባላችሁን አላህም በምትሠሩት ሁሉ ውስጠ ዐዋቂ ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibለከሓዲዎች በነፍሶቻቸው ላይ በክህደት የሚመሰክሩ ሲኾኑ የአላህን መስጊዶች ሊሠሩ አይገባቸውም፡፡ እነዚያ ሥራዎቻቸው ተበላሹ፡፡ እነሱም በእሳት ውስጥ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibየአላህን መስጊዶች የሚሠራው በአላህና በመጨረሻው ቀን ያመነ፣ ሶላትንም በደንቡ የሰገደ፣ ግዴታ ምጽዋትንም የሰጠ ከአላህም ሌላ (ማንንም) ያልፈራ ሰው ብቻ ነው፡፡ እነዚያም ከተመሩት ጭምር መኾናቸው ተረጋገጠ፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibካዕባን ጎብኝዎችን ማጠጣትንና የተከበረውን መስጊድ መሥራትን በአላህና በመጨረሻው ቀን እንዳመነና በአላህ መንገድ እንደታገለ ሰው (እምነትና ትግል) አደረጋችሁን አላህ ዘንድ አይተካከሉም፡፡ አላህም በዳዮች ሕዝቦችን አይመራም፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibእነዚያ ያመኑት፣ ከአገራቸውም የተሰደዱት፣ በገንዘቦቻቸውና በነፍሶቻቸውም በአላህ መንገድ ላይ የታገሉት አላህ ዘንድ በደረጃ በጣም የላቁ ናቸው፡፡ እነዚያም እነሱ ፍላጎታቸውን ያገኙ ናቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibጌታቸው ከርሱ በኾነው እዝነትና ውዴታ በገነቶችም ለነሱ በውስጥዋ የማያቋርጥ መጠቀሚያ ያለባት ስትኾን ያበስራቸዋል፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibበውስጧ ዘላለም ዘውታሪዎች ሲኾኑ (ያበስራቸዋል)፡፡ አላህ እርሱ ዘንድ ታላቅ ምንዳ አለና፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibእናንተ ያመናችሁ ሆይ! አባቶቻችሁና ወንድሞቻችሁ ክህደትን ከእምነት አብልጠው ቢወዱ ወዳጆች አድርጋችሁ አትያዙዋቸው፡፡ ከእናንተም ውስጥ ወዳጅ የሚያደርጋቸው እነዚያ እነሱ በዳዮች ናቸው፤
  1. Sadiq & Sani Habib«አባቶቻችሁና ወንዶች ልጆቻችሁ፣ ወንድሞቻችሁም፣ ሚስቶቻችሁም፣ ዘመዶቻችሁም፣ የሰበሰባችኋቸው ሀብቶችም፣ መክሰሩዋን የምትፈሩዋት ንግድም፣ የምትወዷቸው መኖሪያዎችም እናንተ ዘንድ ከአላህና ከመልክተኛው በርሱ መንገድም ከመታገል ይበልጥ የተወደዱ እንደኾኑ አላህ ትእዛዙን እስከሚያመጣ ድረስ ተጠባበቁ» በላቸው፡፡ አላህም አመጸኞች ሕዝቦችን አይመራም፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibአላህም በብዙ ስፍራዎች በእርግጥ ረዳችሁ፤ የሑነይንም ቀን ብዛታችሁ በአስደነቀቻችሁና ከእናንተም ምንም ባልጠቀመቻችሁ ጊዜ ምድርም ከስፋቷ ጋር በጠበበቻችሁና ከዚያም ተሸናፊዎች ኾናችሁ በዞራችሁ ጊዜ (ረዳችሁ)፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibከዚያም አላህ እርጋታውን በመልክተኛውና በምእምናኖቹ ላይ አወረደ፡፡ ያላያችኋቸውንም ሰራዊት አወረደ፡፡ እነዚያን የካዱትንም በመገደልና በመማረክ አሰቃየ፡፡ ይህም የከሓዲያን ፍዳ ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibከዚያም ከዚህ በኋላ አላህ በሚሻው ሰው ላይ ጸጸትን ይቀበላል፡፡ አላህም እጅግ መሓሪ አዛኝ ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibእናንተ ያመናችሁ ሆይ! አጋሪዎች እርኩሶች ብቻ ናቸው፡፡ ከዚህም ዓመታቸው በኋላ የተከበረውን መስጊድ አይቅረቡ፡፡ ድኽነትንም ብትፈሩ አላህ ቢሻ ከችሮታው በእርግጥ ያከብራችኋል፡፡ አላህ ዐዋቂ ጥበበኛ ነውና፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibከእነዚያ መጽሐፍን ከተሰጡት ሰዎች እነዚያን በአላህና በመጨረሻው ቀን የማያምኑትን፣ አላህና መልክተኛው እርም ያደረጉትንም እርም የማያደርጉትንና እውነተኛውንም ሃይማኖት የማይቀበሉትን እነርሱ የተዋረዱ ኾነው ግብርን በእጆቻቸው እስከሚሰጡ ድረስ ተዋጉዋቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibአይሁድ ዑዘይር የአላህ ልጅ ነው አለች፡፡ ክርስቲያኖችም አልመሲሕ የአላህ ልጅ ነው አሉ፡፡ ይህ በአፎቻቸው (የሚናገሩት) ቃላቸው ነው፡፡ የእነዚያን ከነሱ በፊት የካዱትን ሰዎች ቃል ያመሳስላሉ፡፡ አላህ ያጥፋቸው፡፡ (ከእውነት) እንዴት ይመለሳሉ!
  1. Sadiq & Sani Habibከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የሌለውን አንድን አምላክ ሊገዙ እንጂ ያልታዘዙ ሲኾኑ ሊቃውንቶቻቸውንና መነኮሳታቸውን፣ የመርየምን ልጅ አልመሲሕንም ከአላህ ሌላ አማልክት አድርገው ያዙ፡፡ ከሚያጋሩት ሁሉ የጠራ ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibየአላህን ብርሃን በአፎቻቸው ለማጥፋት ይፈልጋሉ፡፡ አላህም ከሓዲዎች ቢጠሉም እንኳ ብርሃኑን መሙላትን እንጅ ሌላን አይሻም፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibእርሱ ያ አጋሪዎቹ ቢጠሉም መልክተኛውን (ሙሐመድን) በቅን መንገድና በእውነተኛ ሃይማኖት ላይ ከሃይማኖት ሁሉ በላይ ይፋ ያደርገው ዘንድ የላከው ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibእናንተ ያመናችሁ ሆይ! ከሊቃውንትና ከመነኮሳት ብዙዎቹ የሰዎችን ገንዘቦች በውሸት በእርግጥ ይበላሉ፡፡ ከአላህም መንገድ ያግዳሉ፡፡ እነዚያንም ወርቅንና ብርን የሚያደልቡትን በአላህም መንገድ ላይ የማያወጧትን በአሳማሚ ቅጣት አብስራቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibበርሷ ላይ በገሀነም እሳት ውስጥ በሚጋልባትና ግንባሮቻቸውም፣ ጎኖቻቸውም፣ ጀርባዎቻቸውም በርሷ በሚተኮሱ ቀን (አሳማሚ በኾነ ቅጣት አብስራቸው)፡፡ ይህ ለነፍሶቻችሁ ያደለባችሁት ነው፡፡ ታደልቡት የነበራችሁትንም ቅመሱ (ይባላሉ)፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibየወሮች ቁጥር አላህ ዘንድ በአላህ መጽሐፍ ውስጥ ሰማያትንና ምድርን በፈጠረበት ቀን ዐሥራ ሁለት ወር ነው፡፡ ከእነሱ አራቱ የተከበሩ ናቸው፡፡ ይህ ቀጥተኛው ሃይማኖት ነው፡፡ በእነርሱ ውስጥም ነፍሶቻችሁን አትበድሉ፡፡ አጋሪዎችንም በአንድ ላይ ኾነው እንደሚዋጉዋችሁ በአንድ ላይ ኾናችሁ ተጋደሉዋቸው፡፡ አላህም ከሚፈሩት ጋር መኾኑን ዕወቁ፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibየአንዱን ወር ክብር ወደ ሌላው ማዘግየት በክህደት ላይ (ክህደትን) መጨመር ብቻ ነው፡፡ በእርሱ እነዚያ የካዱት ሰዎች ይሳሳቱበታል፡፡ በአንድ ዓመት የተፈቀደ ያደርጉታል፡፡ በሌላው ዓመትም ያወግዙታል፡፡ (ይህ) አላህ ያከበራቸውን ወሮች ቁጥር ሊያስተካክሉ፣ አላህም እርም ያደረገውን የተፈቀደ ሊያደርጉ ነው፡፡ የሥራዎቻቸው መጥፎው ለነርሱ ተዋበላቸው፡፡ አላህም ከሓዲያን ሕዝቦችን አይመራም፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibእናንተ ያመናችሁ ሆይ! በአላህ መንገድ (ለመታገል) ውጡ በተባላችሁ ጊዜ ወደ ምድር የምትወዘፉት ለእናንተ ምን አላችሁ የቅርቢቱን ሕይወት ከመጨረሻይቱ ይበልጥ ወደዳችሁን የቅርቢቱም ሕይወት ጥቅም በመጨረሻይቱ (አንጻር) ጥቂት እንጂ አይደለም፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibለዘመቻ ባትወጡ (አላህ) አሳማሚን ቅጣት ይቀጣችኋል፡፡ ከእናንተ ሌላ የኾኑንም ሕዝቦች ይለውጣል፡፡ በምንም አትጎዱትምም፡፡ አላህም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habib(ነቢዩን) ባትረዱት እነዚያ የካዱት ሕዝቦች የሁለት (ሰዎች) ሁለተኛ ኾኖ (ከመካ) ባወጡት ጊዜ አላህ በእርግጥ ረድቶታል፡፡ ሁለቱም በዋሻው ሳሉ ለጓደኛው አትዘን አላህ ከእኛ ጋር ነውና ባለ ጊዜ አላህም መረጋጋትን በእርሱ ላይ አወረደ፡፡ ባላያችኋቸውም ሰራዊት አበረታው፡፡ የእነዚያንም የካዱትን ሰዎች ቃል ዝቅተኛ አደረገ፡፡ የአላህም ቃል ለእርሷ ከፍተኛ ናት፡፡ አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibቀላሎችም ከባዶችም ኾናችሁ ዝመቱ፡፡ በአላህም መንገድ በገንዘቦቻችሁ በነፍሶቻችሁም ታገሉ፡፡ ይህ የምታውቁ ብትኾኑ ለናንተ በጣም የተሻለ ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habib(የጠራህባቸው ነገር) ቅርብ ጥቅምና መካከለኛ ጉዞ በኾነ ኖሮ በተከተሉህ ነበር፡፡ ግን በነሱ ላይ መንገዲቱ ራቀችባቸው፡፡ «በቻልንም ኖሮ ከእናንተ ጋር በወጣን ነበር» ሲሉ በአላህ ይምላሉ፡፡ ነፍሶቻቸውን ያጠፋሉ፡፡ አላህም እነሱ ውሸታሞች መኾናቸውን በእርግጥ ያውቃል፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibአላህ ከአንተ ይቅር አለ፡፡ እነዚያ እውነተኛዎቹ ላንተ እስከሚገለጹልህና ውሸታሞቹንም እስከምታውቅ ድረስ ለነርሱ (እንዲቀሩ) ለምን ፈቀድክላቸው
  1. Sadiq & Sani Habibእነዚያ በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምኑት በገንዘቦቻቸውና በነፍሶቻቸው ከመታገላቸው (ለመቅረት) ፈቃድን አይጠይቁህም፡፡ አላህም የሚፈሩትን ዐዋቂ ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibፈቃድን የሚጠይቁህ እነዚያ በአላህና በመጨረሻው ቀን የማያምኑት ልቦቻቸውም የተጠራጠሩት ብቻ ናቸው፡፡ እነሱም በጥርጣሬያቸው ውስጥ ይዋልላሉ፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibመውጣትንም ባሰቡ ኖሮ ለርሱ ዝግጅትን ባሰናዱ ነበር፡፡ ግን አላህ (ለመውጣት) እንቅስቃሴያቸውን ጠላ (አልሻውም)፡፡ አሰነፋቸውም፡፡ ከተቀማጮቹም ጋር ተቀመጡ ተባሉ፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibከእናንተ ጋር በወጡ ኖሮ ጥፋትን እንጂ አይጨምሩላችሁም ነበር፡፡ ሁከትንም የሚፈልጉላችሁ ሲኾኑ በመካከላችሁ (በማሳበቅ) ይቻኮሉ ነበር፡፡ በናንተም ውስጥ ለነሱ አዳማጮች አሏቸው፡፡ አላህም በዳዮችን ዐዋቂ ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibእነርሱ ጠይዎች ሲኾኑ እውነቱ እስከመጣና የአላህም ትዕዛዝ እስከተገለጸ ድረስ ከዚህ በፊት ሁከትን በእርግጥ ፈለጉ፡፡ ነገሮችንም ሁሉ አገላበጡልህ፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibከነሱም ውስጥ «ለእኔ ፍቀድልኝ አትሞክረኝም» የሚል ሰው አልለ፡፡ ንቁ! በመከራ ውስጥ ወደቁ፡፡ ገሀነምም ከሓዲዎችን በእርግጥ ከባቢ ናት፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibመልካም ነገር ብታገኝህ ታስከፋቸዋለች፡፡ መከራም ብታገኝህ «ከዚህ በፊት በእርግጥ ጥንቃቄያችንን ይዘናል» ይላሉ፡፡ እነርሱም ተደሳቾች ኾነው ይሸሻሉ፡፡
  1. Sadiq & Sani Habib«አላህ ለኛ የጻፈልን (ጥቅም) እንጂ ሌላ አይነካንም፡፡ እርሱ ረዳታችን ነው፡፡ በአላህ ላይም ምእመናን ይመኩ» በላቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habib«በእኛ ላይ ከሁለቱ መልካሞች አንደኛዋን እንጂ ሌላን ትጠባበቃላችሁን እኛም አላህ ከእርሱ በኾነው ቅጣት ወይም በእጆቻችን የሚያጠፋችሁ መኾኑን በናንተ ላይ እንጠባበቃለን፡፡ ተጠባበቁም እኛ ከእናንተ ጋር ተጠባባቂዎች ነንና» በላቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habib«ወዳችሁም ኾነ ጠልታችሁ ለግሱ፡፡ ከእናንተ ተቀባይ የላችሁም፡፡ እናንተ አመጸኞች ሕዝቦች ናችሁና» በላቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibልግስናዎቻቸውን ከነሱ ተቀባይ የሚያገኙ ከመኾን እነሱ በአላህና በመልክተኛው የካዱ፣ ሶላትንም እነሱ ታካቾች ኾነው በስተቀር የማይሰግዱ፣ እነሱም ጠይዎች ኾነው በስተቀር የማይሰጡ መኾናቸው እንጂ ሌላ አልከለከላቸውም፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibገንዘቦቻቸውና ልጆቻቸውም አይድነቁህ፡፡ አላህ የሚሻው በቅርቢቱ ሕይወት በነርሱ (በገንዘቦቻቸውና በልጆቻቸው) ሊቀጣቸው ነፍሶቻቸውም እነሱ ከሓዲዎች ኾነው ሊወጡ ብቻ ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibእነሱም በእርግጥ ከእናንተ ለመኾናቸው በአላህ ይምላሉ፡፡ እነርሱም ከናንተ አይደሉም፡፡ ግን እነሱ (አጋሪዎችን ያገኘ እንዳያገኛቸው) የሚፈሩ ሕዝቦች ናቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibመጠጊያን ወይም ዋሻዎችን ወይም መግቢያን (ቀዳዳ) ባገኙ ኖሮ እነርሱ እየገሰገሱ ወደርሱ በሸሹ ነበር፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibከነሱም ውስጥ በምጽዋቶች የሚዘልፉህ ሰዎች አሉ፡፡ ከርሷም (የሚሹትን) ቢስሰጡ ይደሰታሉ፡፡ ከርሷም ባይስሰጡ እነሱ ያን ጊዜ ይጠላሉ፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibእነሱም አላህና መልክተኛው የሰጣቸውን በወደዱ፣ «አላህም በቂያችን ነው፤ አላህ ከችሮታው በእርግጥ ይሰጠናል፣ መልክተኛውም (ይሰጠናል)፣ እኛ ወደ አላህ ከጃዮች ነን» ባሉ ኖሮ (ለነሱ በተሻላቸው ነበር)፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibግዴታ ምጽዋቶች (የሚከፈሉት) ለድኾች፣ ለምስኪኖችም፣ በርሷም ላይ ለሚሠሩ ሠራተኞች፣ ልቦቻቸውም (በእስልምና) ለሚለማመዱት፣ ጫንቃዎችንም (በባርነት ተገዢዎችን) ነጻ በማውጣት፣ በባለ ዕዳዎችም፣ በአላህ መንገድም በሚሠሩ፣ በመንገደኛም ብቻ ነው፡፡ ከአላህ የተደነገገች ግዴታ ናት፡፡ አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibከእነሱም (ከመናፍቃን) እነዚያ ነቢዩን የሚያሰቃዩ «እርሱም ጆሮ ነው» (ወሬ ሰሚ ነው) የሚሉ አልሉ በላቸው፡፡ ለእናንተ የበጎ (ወሬ) ሰሚ ነው፡፡ በአላህ ያምናል፣ ምእምናንንም ያምናቸዋል፣ ከእናንተም ውስጥ ለነዚያ ላመኑት እዝነት ነው፡፡ እነዚያም የአላህን መልክተኛ የሚያሰቃዩ ለነሱ አሳማሚ ቅጣት አላቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibአላህንና መልክተኛውን ሊያስወድዱ ተገቢያቸው ሲኾን እናንተን ያስወደዷችሁ ዘንድ በአላህ ይምሉላችኋል፡፡ ምእምናኖች ቢኾኑ (አላህንና መልክተኛውን ያስወድዱ)፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibአላህንና መልክተኛውን የሚከራከር ሰው ለእርሱ የገሀነም እሳት በውስጧ ዘውታሪ ሲኾን የተገባቺው መኾኑን አያውቁምን ይህ ታላቅ ውርደት ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibመናፍቃን በልቦቻቸው ውስጥ ያለውን ነገር የምትነግራቸው ሱራ በእነርሱ ላይ መውረዷን ይፈራሉ፡፡ «አላግጡ አላህ የምትፈሩትን ሁሉ ገላጭ ነው» በላቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibበእርግጥ ብትጠይቃቸው «እኛ የምንዘባርቅና የምንጫወት ብቻ ነበርን» ይላሉ፡፡ «በአላህና በአንቀጾቹ፣ በመልክተኛውም ታላግጡ ነበራችሁን» በላቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibአታመካኙ፤ ከእምነታችሁ በኋላ በእርግጥ ካዳችሁ፡፡ ከእናንተ አንዷን ጭፍራ ብንምር (ሌላዋን) ጭፍራ እነሱ ኃጢአተኞች በመኾናቸው እንቀጣለን፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibመናፍቃንና መናፍቃት ከፊሎቻቸው ከከፊሉ ናቸው፡፡ በመጥፎ ነገር ያዛሉ ከደግም ነገር ይከለክላሉ፡፡ እጆቻቸውንም (ከልግስና) ይሰበስባሉ፡፡ አላህን ረሱ፡፡፤ ስለዚህ (እርሱ) ዋቸው፡፡ መናፍቃን አመጸኞቹ እነሱ ናቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibመናፍቃንንና መናፍቃትን፣ ከሓዲዎችንም አላህ የገሀነምን እሳት በውስጧ ዘውታሪዎች ሲኾኑ ቃል ገብቶላቸዋል፡፡ እርሷ በቂያቸው ናት፡፡ አላህም ረግሟቸዋል፡፡ ለእነርሱም ዘውታሪ ቅጣት አላቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibእንደነዚያ ከናንተ በፊት እንደ ነበሩት ናችሁ፡፡ ከእናንተ ይበልጥ በኃይል የበረቱ በገንዘቦችም በልጆችም ይበልጥ የበዙ ነበሩ፡፡ በዕድላቸውም ተጠቀሙ፡፡ እነዚያም ከእናንተ በፊት የነበሩት በዕድላቸው እንደተጠቀሙ በዕድላችሁ ተጠቀማችሁ፡፡ እንደነዚያም እንደዘባረቁት ዘባረቃችሁ፡፡ እነዚያ ሥራዎቻቸው በቅርቢቱም በመጨረሻይቱም ዓለም ተበላሹ፡፡ እነዚያም ከሳሪዎቹ እነሱ ናቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibየእነዚያ ከእናንተ በፊት የነበሩት የኑሕ ሕዝቦች፣ የዓድና የሰሙድም፣ የኢብራሂምም ሕዝቦች የመድየን ባለቤቶችና የተገልባጮቹም ከተሞች ወሬ አልመጣላቸውምን መልክተኞቻቸው በተዓምራት መጧቸው፡፡ አላህም የሚበድላቸው አልነበረም፡፡ ግን ነፍሶቻቸውን የሚበድሉ ነበሩ፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibምእምንና ምእምናትም ከፊሎቻቸው ለከፊሉ ረዳቶች ናቸው፡፡ በደግ ነገር ያዛሉ፤ ከክፉም ይከለክላሉ፡፡ ሶላትንም ይሰግዳሉ፡፡ ዘካንም ይሰጣሉ፡፡ አላህንና መልክተኛውንም ይታዘዛሉ፡፡ እነዚያን አላህ በእርግጥ ያዝንላቸዋል፡፡ አላህ አሸናፊ ጥበበኛ ነውና፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibአላህ ምእምናንንና ምእምናትን ከሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች በውስጣቸው ዘውታሪዎች ሲኾኑ በመኖሪያ ገነቶችም ውስጥ መልካም መኖሪያ ቤቶችን ቃል ገብቶላቸዋል፡፡ ከአላህም የኾነው ውዴታ ከሁሉ የበለጠ ነው፡፡ ይህ እርሱ ታላቅ እድል ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibአንተ ነቢዩ ሆይ! ከሓዲዎችንና መናፍቃንን ታገል፡፡ በእነሱም ላይ ጨክን፡፡ መኖሪያቸውም ገሀነም ናት፡፡ መመለሻይቱም ከፋች፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibምንም ያላሉ ለመኾናቸው በአላህ ይምላሉ፡፡ የክህደትንም ቃል በእርግጥ አሉ፡፡ ከእስልምናቸውም በኋላ ካዱ፡፡ ያላገኙትንም ነገር አሰቡ፡፡ አላህም ከችሮታው መልክተኛውም (እንደዚሁ) ያከበራቸው መኾኑን እንጂ ሌላን አልጠሉም፡፡ ቢጸጸቱም ለእነሱ የተሻለ ይኾናል፡፡ ቢሸሹም አላህ በቅርቢቱና በመጨረሻይቱ ዓለም አሳማሚን ቅጣት ይቀጣቸዋል፡፡ ለእነሱም በምድር ውስጥ ምንም ወዳጅና ረዳት የላቸውም፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibከእነሱም «አላህን ከችሮታው ቢሰጠን በእርግጥ እንመጸውታለን ከመልካሞቹም በእርግጥ እንኾናለን» ሲል ቃል የተጋባ አልለ፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibከችሮታውም በሰጣቸው ጊዜ በእርሱ ሰሰቱ፡፡ እነሱ (ኪዳናቸውን) የተዉ ኾነውም ዞሩ፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibአላህንም ቃል የገቡለትን በማፍረሳቸውና ይዋሹትም በነበሩት ምክንያት እስከሚገናኙት ቀን ድረስ ንፍቅናን አስከተላቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibአላህ ምስጢራቸውንና ውይይታቸውን የሚያውቅ መኾኑን አላህም ሩቆችን ሁሉ በጣም ዐዋቂ መኾኑን አያውቁምን
  1. Sadiq & Sani Habibእነዚያ ከምእምናን በምጽዋቶች ፈቃደኛ የኾኑትን፣ እነዚያንም የችሎታቸውን ያክል እንጅ የማያገኙትን ሰዎች የሚያነውሩ፣ ከእነሱም የሚስቁ አላህ ከነሱ ይሳለቅባቸዋል፤ (ይቀጣቸዋል)፡፡ ለእነሱም አሳማሚ ቅጣት አላቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibለእነርሱ ምሕረትን ለምንላቸው፤ ወይም ለእነሱ ምሕረትን አትለምንላቸው (እኩል ነው)፡፡ ለእነሱ ሰባ ጊዜ ምሕረትን ብትለምንላቸው አላህ ለነሱ በፍጹም አይምርም፡፡ ይህ እነርሱ አላህና መልክተኛውን በመካዳቸው ነው፡፡ አላህም አመጸኞች ሕዝቦችን አያቀናም፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibእነዚያ ከዘመቻ የቀሩት ከአላህ መልክተኛ በኋላ በመቀመጣቸው ተደሰቱ፡፡ በአላህም መንገድ በገንዘቦቻቸውና በነፍሶቻቸው መታገልን ጠሉ፡፡ «በሐሩር አትኺዱ» አሉም፡፡ «የገሀነም እሳት ተኳሳነቱ በጣም የበረታ ነው» በላቸው፡፡ የሚያውቁ ቢኾኑ ኖሮ (አይቀሩም ነበር)፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibጥቂትንም ይሳቁ፡፡ ይሠሩት በነበሩት ዋጋ ብዙን ያለቅሳሉ፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibከእነሱም ወደ ኾነችው ጭፍራ አላህ ቢመልስህ (ከአንተ ጋር) ለመውጣትም ቢያስፈቅዱህ፡-«ከኔ ጋር በፍጹም አትወጡም፡፡ ከእኔም ጋር ጠላትን አትዋጉም፡፡ እናንተ በመጀመሪያ ጊዜ መቀመጥን ወዳችኋልና፡፡ ከተቀማጮቹ ጋርም ተቀመጡ» በላቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibከእነሱም በአንድም በሞተ ሰው ላይ ፈጽሞ አትስገድ፡፡ በመቃብሩም ላይ አትቁም፡፡ እነሱ አላህንና መልክተኛውን ክደዋልና፡፡ እነሱም አመጸኞች ኾነው ሞተዋልና፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibገንዘቦቻቸውና ልጆቻቸውም አይድነቁህ፡፡ አላህ የሚሻው በቅርቢቱ ዓለም በነሱ ሊቀጣቸውና ከሓዲዎችም ኾነው ነፍሶቻቸው እንዲወጡ ብቻ ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibበአላህ እመኑ፡፡ ከመልክተኛውም ጋር ኾናችሁ ታገሉ፤ በማለት ምዕራፍ በተወረደች ጊዜ ከነሱ የሰፊ ሀብት ባለቤቶች የኾኑት (ለመቅረት) ፈቃድ ይጠይቁሃል፡፡ «ከተቀማጮቹ ጋርም እንኹን ተወን» ይሉሃል፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibበቤት ከሚቀሩት ጋር መኾናቸውን ወደዱ፡፡ በልቦቻቸውም ላይ (ዝገት) ታተመባቸው፡፡ ስለዚህ እነሱ አያውቁም፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibግን መልክተኛው እነዚያም ከርሱ ጋር ያመኑት በገንዘቦቻቸውም በነፍሶቻቸውም ታገሉ፡፡ እነዚያም መልካሞች ሁሉ ለነሱ ናቸው፡፡ እነዚያም እነሱ ምኞታቸውን ያገኙ ናቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibለእነሱም ገነቶችን በሥራቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን በውስጣቸው ዘውታሪዎች ሲኾኑ አላህ አዘጋጅቶላቸዋል፡፡ ይህ ታላቅ ማግኘት ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibከአዕራቦችም ይቅርታ ፈላጊዎቹ ለእነሱ እንዲፈቀድላቸው መጡ፡፡ እነዚያ አላህንና መልክተኛውን የዋሹትም ተቀመጡ፡፡ ከነሱ እነዚያን የካዱትን አሳማሚ ቅጣት በእርግጥ ይነካቸዋል፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibበደካሞች ላይ በበሽተኞችም ላይ በነዚያም የሚያወጡት ገንዘብ በማያገኙት ላይ ለአላህና ለመልክተኛው ፍጹም ታዛዦች ከኾኑ (ባይወጡም) ኃጢኣት የለባቸውም፡፡ በበጎ አድራጊዎች ላይ (የወቀሳ) መንገድ ምንም የለባቸውም፡፡ አላህም መሓሪ አዛኝ ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibበእነዚያም ልትጭናቸው በመጡህ ጊዜ «በርሱ ላይ የምጭናችሁ (አጋሰስ) አላገኝም፤» ያልካቸው ስትኾን የሚያወጡት ገንዘብ ባለማግኘታቸው ለማዘናቸው ዓይኖቻቸው እንባን እያፈሰሱ በዞሩት ላይ (የወቀሳ መንገድ የለባቸውም)፡፡
  1. Sadiq & Sani Habib(የወቀሳ) መንገዱ በእነዚያ እነሱ ባለጸጋዎች ኾነው ሳሉ ለመቅረት ፈቃድ በሚጠይቁህ ሰዎች ላይ ብቻ ነው፡፡ ከቀሪዎቹ ጋር መኾናቸውን ወደዱ፡፡ አላህም በልቦቻቸው ላይ አተመባቸው፤ ስለዚህ እነሱ አያውቁም፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibወደእነሱ በተመለሳችሁ ጊዜ ምክንያታቸውን ያቀርቡላችኋል፡፡ አታመካኙ፤ እናንተን ፈጽሞ አናምንም፡፡ አላህ ከወሬዎቻችሁ በእርግጥ ነግሮናልና፡፡ አላህም ሥራችሁን በእርግጥ ያያል፡፡ መልክተኛውም (እንደዚሁ)፤ ከዚያም ሩቅንና ቅርብን ሁሉ ዐዋቂ ወደ ኾነው (አላህ) ትመለሳላችሁ ወዲያውም ትሠሩት የነበራችሁትን ሁሉ ይነግራችኋል በላቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibወደእነሱ በተመለሳችሁ ጊዜ እንድትተውዋቸው ለእናንተ በእርግጥ በአላህ ይምላሉ፡፡ እነሱንም ተዋቸው፡፡ እነሱ እርኩሶች ናቸውና፡፡ ይሠሩትም በነበሩት ዋጋ መኖሪያቸው ገሀነም ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibከእነሱ ትወዱላቸው ዘንድ ለናንተ ይምሉላችኋል፡፡ ከእነሱ ብትወዱም አላህ አመጸኞች ሕዝቦችን አይወድም፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibአዕራቦች በክህደትና በንፍቅና በጣም የበረቱ፤ አላህም በመልክተኛው ላይ ያወረደውን ሕግጋት ባለማወቅ የተገቡ ናቸው፡፡ አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibከአዕራቦችም (በአላህ መንገድ) የሚወጣውን (ገንዘብ) ዕዳ አድርጎ የሚይዝ በእናንተም ላይ የጊዜን መገለባበጥ የሚጠባበቅ ሰው አልለ፡፡ በእነሱ ላይ ጥፋቱ ይዙርባቸው፡፡ አላህም ሰሚ ዐዋቂ ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibከአዕራቦችም በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምን የሚሰጣቸውንም (ምጽዋቶች) አላህ ዘንድ መቃረቢያዎችና ወደ መልክተኛው ጸሎቶች መዳረሻ አድርጎ የሚይዝ ሰው አልለ፡፡ ንቁ! እርሷ ለእነሱ በእርግጥ አቃራቢ ናት፡፡ አላህ በችሮታው ውስጥ (በገነቱ) በእርግጥ ያስገባቸዋል፡፡ አላህ መሓሪ አዛኝ ነውና፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibከስደተኞቹና ከረዳቶቹም ሲኾኑ የመጀመሪያዎቹ ቀዳሚዎች እነዚያም በበጎ ሥራ የተከተሏቸው አላህ ከእነሱ ወዷል ከእርሱም ወደዋል፡፡ በሥሮቻቸውም ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች በውስጣቸው ዘለዓለም ነዋሪዎች ሲኾኑ ለእነርሱ አዘጋጅቶላቸዋል፡፡ ይህ ታላቅ ዕድል ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibበዙሪያችሁም ካሉት ከዐረብ ዘላኖች መናፍቃን አልሉ፡፡ ከመዲና ሰዎችም በንፍቅና ላይ በማመጽ የዘወተሩ አልሉ፡፡ አታውቃቸውም፡፡ እኛ እናውቃቸዋለን፡፡ ሁለት ጊዜ እንቀጣቸዋለን፡፡ ከዚያም ወደታላቅ ቅጣት ይመለሳሉ፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibሌሎችም በኃጢአቶቻቸው የተናዘዙ መልካም ሥራንና ሌላን መጥፎ ሥራ የቀላቀሉ አልሉ፡፡ አላህ ከእነሱ ጸጸታቸውን ሊቀበል ይከጀላል፡፡ አላህ መሓሪ አዛኝ ነውና፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibከገንዘቦቻቸው ስትኾን በእርሷ የምታጠራቸውና የምታፋፋቸው የኾነችን ምጽዋት ያዝ፡፡ ለነሱም ጸልይላቸው፡፡ ጸሎትህ ለእነሱ እርጋታ ነውና አላህም ሰሚ ዐዋቂ ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibአላህ እርሱ ከባሮቹ ንስሓን የሚቀበል ምጽዋቶችንም የሚወስድ መኾኑን አላህም እርሱ ጸጸትን ተቀባይ አዛኝ መኾኑን አያውቁም
  1. Sadiq & Sani Habibበላቸውም ሥሩ አላህ ሠራችሁን በእርግጥ ያያልና፡፡ መልክተኛውና ምእምናንም (እንደዚሁ ያያሉ)፡፡ ሩቁንና ቅርቡን ሁሉ ዐዋቂ ወደ ኾነውም (አላህ) በእርግጥ ትመለሳላችሁ፡፡ ትሠሩትም የነበራችሁትን ሁሉ ይነግራችኋል፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibሌሎችም ለአላህ ትዕዛዝ የተቆዩ ሕዝቦች አልሉ፡፡ ወይ ይቀጣቸዋል ወይም ከነሱ ላይ ጸጸትን ይቀበላል፡፡ አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibእነዚያም (ምእምናንን) ለመጉዳት፣ ክህደትንም ለማበርታት፣ በምእምናንም መካከል ለመለያየት፣ ከአሁን በፊት አላህንና መልክተኛውን የተዋጋውንም ሰው ለመጠባበቅ መስጊድን የሠሩት (ከነሱ ናቸው)፡፡ መልካምን ሥራ እንጂ ሌላ አልሻንም ሲሉም በእርግጥ ይምላሉ፡፡ አላህም እነሱ በእርግጥ ውሸታሞች መኾናቸውን ይመሰክራል፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibበእርሱ ውስጥ በፍጹም አትስገድ፡፡ ከመጀመሪያ ቀን ይዞ በአላህ ፍራቻ ላይ የተመሠረተው (የቁባ) መስጊድ በውስጡ ልትሰግድበት ይልቅ የተገባው ነው፡፡ በእሱ ውስጥ መጥራራትን የሚወዱ ወንዶች አልሉ፡፡ አላህም ተጥራሪዎችን ይወዳል፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibአላህን በመፍራትና ውዴታውን በመፈለግ ላይ ግንቡን የመሠረተው ሰው ይበልጣልን ወይስ ጎርፍ በሸረሸረው ለመናድ በተቃረበ ገደል አፋፍ ላይ ግንቡን የመሠረተውና በርሱ (ይዞት) በገሀነም እሳት ውስጥ የወደቀ (ይበልጣል)፡፡ አላህም በደለኞች ሕዝቦችን አይመራም፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibያ የካቡት ግንባቸው ልቦቻቸው (በሞት) ካልተቆራረጡ በቀር በልቦቻቸው ውስጥ የመጠራጠር ምክንያት ከመኾን አይወገድም፡፡ አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibአላህ ከምእምናን ነፍሶቻቸውንና ገንዘቦቻቸውን ገነት ለእነሱ ብቻ ያላቸው በመኾን ገዛቸው፡፡ በአላህ መንገድ ላይ ይጋደላሉ፡፡ ይገድላሉም፤ ይገደላሉም፡፡ በተውራት በኢንጅልና በቁርኣንም (የተነገረውን) ተስፋ በእርሱ ላይ አረጋገጠ፡፡ ከአላህም የበለጠ በኪዳኑ የሚሞላ ማነው በዚያም በእርሱ በተሻሻጣችሁበት ሽያጫችሁ ተደሰቱ፡፡ ይህም እርሱ ታላቅ ዕድል ነው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habib(እነርሱ) ተጸጻቺዎች፣ ተገዢዎች፣ አመስጋኞች፣ ጿሚዎች፣ አጎንባሾች፣ በግንባር ተደፊዎች፣ በበጎ ሥራ አዛዦች ከክፉም ከልካዮች፣ የአላህንም ሕግጋት ጠባቂዎች ናቸው ምእምናንንም አብስር፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibለነቢዩና ለነዚያ ላመኑት ለአጋሪዎቹ የዝምድና ባለቤቶች ቢኾኑም እንኳ እነሱ (ከሓዲዎቹ) የእሳት ጓዶች መኾናቸው ከተገለጸላቸው በኋላ ምሕረትን ሊለምኑ የሚገባ አልነበረም፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibየኢብራሂምም ለአባቱ ምሕረትን መለመን ለእርሱ ገብቶለት ለነበረችው ቃል (ለመሙላት) እንጂ ለሌላ አልነበረም፡፡ እርሱም የአላህ ጠላት መኾኑ ለእርሱ በተገለጸለት ጊዜ ከርሱ ራቀ፤ (ተወው)፡፡ ኢብራሂም በእርግጥ በጣም ርኅሩኅ ታጋሽ ነውና፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibአላህም ሕዝቦችን ከአቀናቸው በኋላ የሚጠነቀቁትን (ሥራ) ለእነሱ እስከሚገልጸላቸው (እስከሚተውትም) ድረስ ጥፋተኛ የሚያደርግ አይደለም፡፡ አላህ በነገሩ ሁሉ ዐዋቂ ነውና፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibአላህ የሰማያትና የምድር ንግስና የርሱ ብቻ ነው፡፡ ሕያው ያደርጋል፤ ይገድላልም፡፡ ለእናንተም ከርሱ በቀር ጠባቂም ረዳትም የላችሁም፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibበነቢዩ በነዚያም በችግሪቱ ጊዜያት (በተቡክ ዘመቻ) ከእነሱ የከፊሎቹ ልቦች (ለመቅረት) ሊዘነበሉ ከተቃረቡ በኋላ በተከተሉት ስደተኞችና ረዳቶች ላይ አላህ በእርግጥ ጸጸታቸውን ተቀበለ፡፡ ከዚያም ከእነሱ ንስሓ መግባታቸውን ተቀበለ፡፡ እርሱ ለእነሱ ርኅሩኅ አዛኝ ነውና፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibበእነዚያም በሦስቱ ሰዎች ላይ ምድር ከስፋትዋ ጋር በእነሱ ላይ እስከ ጠበበች፣ ነፍሶቻቸውም በርሳቸው ላይ እስከተጠበቡ፣ ከአላህም ወደርሱ ቢኾን እንጂ ሌላ መጠጊያ አለመኖሩን እስከ አረጋገጡ ድረስ በተቆዩት ላይ (አላህ ጸጸትን ተቀበለ)፡፡ ከዚያም ይጸጸቱ ዘንድ ወደ ጸጸት መራቸው፡፡ አላህ እርሱ ጸጸትን ተቀባይ አዛኝ ነውና፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibእናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ፍሩ፤ ከእውነተኞቹም ጋር ኹኑ፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibለመዲና ሰዎችና ከአዕራብም በዙሪያቸው ላሉት ሰዎች ከአላህ መልክተኛ ወደኋላ ሊቀሩ ነፍሶቻቸውንም ከነፍሱ አብልጠው ሊወዱ አይገባቸውም ነበር፡፡ ይህ (ከመቅረት መከልከል) ለእነርሱ መልካም ሥራ የሚጻፍላቸው ቢኾን እንጅ፡፡ በአላህ መንገድ ላይ ጥምም፣ ድካምም፣ ረኃብም፣ የማይነካቸው ከሐዲዎችንም የሚያስቆጭን ስፍራ የማይረግጡ፣ ከጠላትም የሚጎዳን ነገር (መግደልን መማረክን መዝረፍን) የማያገኙ በመኾናቸው ነው፡፡ አላህ የመልካም ሠሪዎችን ምንዳ አያጠፋምና፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibትንሽንም ትልቅንም ልግስና አይለግሱም ወንዝንም አያቋርጡም አላህ ይሠሩት ከነበረው የበለጠን ምንዳ ይመነዳቸው ዘንድ ለእነሱ የሚጻፍላቸው ቢሆን እንጅ፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibምእምናንም (ከነቢዩ ጋር ካልኾነ) በሙሉ ሊወጡ አይገባም፡፡ ከእነሱ ውስጥ ከየክፍሉ አንዲት ጭፍራ ለምን አትወጣም፡፡ (ሌሎቹ) ሃይማኖትን እንዲማሩና ወገኖቻቸው ወደነርሱ በተመለሱ ጊዜ እንዲጠነቀቁ ይገስጹዋቸው ዘንድ (ለምን አይቀሩም)፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibእናንተ ያመናችሁ ሆይ! እነዚያን በአቅራቢያችሁ ያሉትን ከሓዲዎች ተዋጉ፡፡ ከእናንተም ብርታትን ያግኙ፡፡ አላህም ከሚጠነቀቁት ጋር መኾኑን ዕወቁ፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibሱራም (ምዕራፍ) በተወረደች ጊዜ ከእነሱ (ከመናፍቃን) ውስጥ ማንኛችሁ ነው ይህች (ምዕራፍ) እምነትን የጨመረችለት የሚል ሰው አልለ፡፡ እነዚያ ያመኑትማ የሚደሰቱ ሲኾኑ እምነትን ጨመረችላቸው፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibእነዚያም በልቦቻቸው ውስጥ በሽታ ያለባቸውማ በርክሰታቸው ላይ ርክሰትን ጨመረችላቸው፡፡ እነርሱም ከሓዲዎች ኾነው ሞቱ፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibበየዓመቱ አንድ ወይም ሁለት ጊዜ እነርሱ የሚሞከሩ መኾናቸውን አያዩምን ከዚያም አይጸጸቱምን እነሱም አይገሰጹምን
  1. Sadiq & Sani Habib(እነሱን የምታነሳ) ምዕራፍም በተወረደች ጊዜ አንድ ሰው ያያችኋልን እያሉ ከፊሎቻቸው ወደ ከፊሉ ይመለከታሉ፡፡ ከዚያም (ተደብቀው) ይኼዳሉ፡፡ እነርሱ የማያውቁ ሕዝቦች በመኾናቸው አላህ ልቦቻቸውን አዞረ፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibከጎሳችሁ የሆነ ችግራችሁ በእርሱ ላይ ጽኑ የሆነ፣ በእናንተ (እምነት) ላይ የሚጓጓ፣ በምእምናን (ላይ) ርኅሩኅ አዛኝ የኾነ መልክተኛ በእርግጥ መጣላችሁ፡፡
  1. Sadiq & Sani Habibቢያፈገፍጉም አላህ በቂዬ ነው፡፡ ከእርሱ ሌላ አምላክ የለም፡፡ በእርሱ ላይ ተጠጋሁ እርሱም የታላቁ ዐርሽ ጌታ ነው በላቸው፡፡